«ለወራት ክስ ሳይመሰረትብኝ፣ ፍ/ቤትም ሳልቀርብ በግፍ ታስሬያለሁ›› ማሩ ዳኜ፣ ከባ/ዳር እስር ቤት

ስም፡- ማሩ ዳኜ

ዕድሜ፡- 36

አድራሻ፡- ባህር ዳር ከተማ

አሁን በእስር የምገኝበት ቦታ፡- ‹በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ

ለእስር የተዳረግሁበት ምክንያት፡- ነሐሴ 01/2008 ዓ.ም በዚሁ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ተደርጎ የነበረውን የተቃውሞ ህዝባዊ ሰልፍ ጠርተሃል፣ አስተባብረሃል በሚል ነው፡፡

በይፋ የተመሰረተብኝ የክስ አይነት፡- ለእስር ከተዳረግሁበት ነሐሴ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በይፋ ክስ አልተመሰረተብኝም፡፡ ሆኖም ግን የክልሉ ፍትህ ቢሮ እኔንና አብረውኝ የታሰሩትን ሰዎች ለ11 ሰዎች ህይወት መጥፋት፣ ለ59 ሰዎች አካል ጉዳት እና ለ29 ሚሊዮን ብር ውድመት ተጠያቂነት ስለሚጠረጠሩ በሚል ዋስትናችን እንዲነፈግ ለክልል ጠ/ፍርድ ቤት በጽሁፍ አቤቱታ ቀርቦ በእስር ላይ መገኘቴን አውቃለሁ፡፡

በእስር በምገኝበት ወቅት የሚከተሉት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡

  1. ያለምንም ይፋዊ ክስ ለረጂም ወራት ታስሬያለሁ፡፡
  2. በመደበኛነት ፍርድ ቤት መቅረብ አልቻልሁም፡፡ ይህም ያለኝን አቤቱታ የማሰማት እድል ነፍጎኛል፡፡
  3. ለእስር ስዳረግ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታፍኜ ነው የታሰርሁት፡፡
  4. ስድብና ዛቻ ደርሶብኛል፡፡
  5. የታሰርሁት ካስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ በፊት ቢሆንም በአዋጁ ሰበብ ጠበቃ እንኳ እንዳላገኝ ተደርጌ ታስሬያለሁ፡፡
  6. ከፍተኛ ሙቀት ባለበት ክፍል ውስጥ በአንድ አልጋ ላይ አራት ሰዎች ጋር እንድተኛ ተገድጃለሁ፡፡

የኋላ ታሪክ:

በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነኝ፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በህጋዊነት ተመዝግበው የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሚያደርጉ ሦስት ፓርቲዎች (ቅንጅት፣ አንድነት እና ሰማያዊ) ውስጥ አባል በመሆን የፖለቲካ አራማጅ ሆኜ ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ስለሰው ልጆች መብት መከበር በመናገሬ፣ በመታገሌ ከደስታ ውጭ የሚሰማኝ ነገር የለም፡፡ በዚህ ድርጊቴ ለአፍታ እንኳ እስር ቤት መግባት አልነበረብኝም፡፡

የሦስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ እስከታሰርሁ ድረስ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየሰራሁ፣ በዚያውም ራሴን ለማሻሻል በዚሁ ተቋም እየተማርሁ ነበር፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *