‹‹ለ12 ቀናት ቀዝቃዛ ባዶ ሲሚንቶ ወለል ላይ እንድተኛ ተደርጌያለሁ›› የኦፌኮ አመራር አቶ ደስታ ዲንቃ

ስም፡– ደስታ ዲንቃ ጎሴ
ዕድሜ፡- 42 አመት
አድራሻ፡- ኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ዞን ሱሉልታ ወሰርቢ ቀበሌ
አሁን በእስር የምገኝበት ቦታ፡- ቂሊንጦ እስር ቤት
ለእስር የተዳረግሁበት ምክንያት፡- በሽብር ተከስሼ (በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው ህዝባዊ የመብት ጥያቄ ወቅት አመጽ አነሳስተሃል፣ አደራጅተሃል በሚል)
በይፋ የተመሰረተብኝ የክስ አይነት፡- በ25/09/08 ዓ.ም በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ቀርቦብኝ ጉዳየን እየተከታተልሁ ነው፡፡ አቃቤ ህግ የጸረ-ሽብር አዋጁን አንቀጽ 4 እና 3(1)/3(2)/3(4) እና 3(6)ን በመተላለፍ ክስ አቅርቦብኛል፡፡ በዚህም፣ በሌላ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ከቀረበባቸው እነ ጉርሜሳ አያኖ ጋር በመሆን ኦፌኮን እንደሽፋን በመጠቀም ከኦነግ ጋር በህቡህ ግንኙነት በመፍጠር ሁከትና አመጽ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ነው የከሰሱኝ፡፡ ጉዳዩን የሚያየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡
በእስር በምገኝበት ወቅት የሚከተሉት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡፡
1. በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በቆየሁበት ጊዜ በታሰርሁ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ጠያቂ ተከልክያለሁ፡፡
2. በተጠረጠርሁበት የሽብር ወንጀል፣ የጸረ-ሽብር አዋጁ ከሚፈቅደው የምርመራ ጊዜ በተጻራሪ ከአምስት ወራት በላይ በምርመራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡
3. በቂ የጸሐይ ብርሃንና ንጹህ አየር እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ፡፡
4. በ2008 ዓ.ም መጨረሻ በታሰርሁበት ቂሊንጦ እስር ቤት ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ በነበረው ጊዜ ቃጠሎውን ተከትሎ ወደሌሎች እስር ቤቶች እንዲዛወሩ ከተደረጉት መካከል ስሆን፣ ወደዝዋይ የፌደራል ማ/ቤት ተወስጄ ለ12 ቀናት ባዶ ሲሚንቶ ላይ እንድተኛ ተገድጃለሁ፡፡
5. ዝዋይ እያለሁ እጆቼ ከአንድ እስረኛ ጋር ተጣምረው ታስሬ ነበር የምውለውና የማድረው፡፡
6. አንድ ቀን የታሰርሁበት ሰንሰለት በራሱ ጊዜ ተፈትቶ፣ ‹ስለምን ፈታኸው!› ተብዬ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞብኛል፡፡
7. ጠያቂ ተከልክየ ቤተሰቦቼን ሳላይ እንዳሳልፍ ተደርጌያለሁ፡፡
ባለትዳርና የቤተሰብ ኃላፊ ነኝ፤ ልጆች አሉኝ፡፡ የምወዳቸው እናቴ በእስር ቤት ሆኜ አርፈዋል፤ አልቅሼ መቅበር አልቻልሁም፡፡
በሙያዬ ደግሞ የህግ ባለሙያ ነኝ፡፡ በኦፌኮ ፓርቲ ውስጥ የህግ ክፍሉ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ በ2006 ዓ.ም በአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ዞን ሊተገበር የታቀደውን ‹ማስተር ፕላን› በመቃወም በአምቦና በወለጋ አካባቢዎች ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው ለእስር ሲዳረጉ የህግ ድጋፍ እሰጥ ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ በህጋዊነት እውቅና አግኝተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሚያደርጉት የኦፌኮ እና ኦፌኮ አባል በሆነበት መድረክ ፓርቲዎች ውስጥ በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ ተሳትፎ አደርጋለሁ፡፡ በተለይም በወጣቶች ጉዳይ ኃላፊነትና በኦዲትና ኢንስፔክሽን በጸሐፊነት ሰርቻለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *