‹በማዕካላዊ ለሦስት ቀናት ያለዕረፍት አንጠልጥለው (ሰቅለው) አሰቃይተውኛል›› አወቀ አባተ

ስም፡- አወቀ አባተ ገበየሁ
ዕድሜ፡- 31 ዓመት
አድራሻ፡-አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05
አሁን የምገኝበት፡- ቂሊንጦ እስር ቤት
ለእስር የተዳረግሁበት ምክንያት፡- በሽብርተኝነት ተጠርጥረሃል የሚል ነው፡፡
የቀረበብኝ የክስ ዓይነት፡- የሽብር ክስ ነው፡፡ በዋናነት የጸረ-ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3፣ 4 እና 6 ላይ የተመለከቱትን ድርጊቶች ተላልፈሃል የሚል ነው፡፡ ከሳሼ የፌደራል አቃቤ ህግ ነው፡፡
በእስር ላይ ሆኜ የሚከተሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡፡
1. በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ቀዝቃዛና ጨለማ ክፍል ውስጥ አስረውኛል፡፡
2. በአብዛኛው መለዮ ለባሽ ሴት መርማሪ እጄንና እግሬን በሰንሰለት ታስሬ እንድቀርብላት እየተደረግሁ ደብደባኛለች
3. ይኸችው መርማሪ ሱሪዬን እያወለቀች ብልቴን እየነካካች፣ በምርመራ ክፍሉ ውስጥ ውሃ ሞልታ ያስቀመጠችውን ኮዳ (የሃይላድ ፕላስቲክ) እያሳየች፣ ያን ኮዳ እዚህ ጋር ነው የማንጠለጥለው! ብትናገር ይሻልሃል! እያለች ዛቻ ፈጽማብኛለች፡፡ አሳቃኛለች፤ አስፈራርታኛለች፡፡
4. ጺሜን እየነጨች አሰቃይታኛለች፡፡
5. ድብደባው ከተፈጸመብኝ በኋላም እጅና እግሬ እንደታሰረ ክፍሉ ውስጥ ለረጂም ሰዓታት በመተው አሰቃይታኛለች፡፡
6. በተደጋጋሚ እጅና እግሬ ታስሮ በሆዴ እንድተኛ ተደርጌ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጸመብኝ፡፡ አንድ መርማሪ በሹል ጫማ ወገቤን የመታኝ እስካሁን ለስቃይ እንደዳረገኝ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ገመድም ደብድበውኛል፡፡
7. የማላውቀውን ነገር እየጠየቁ፣ ‹አሁንስ ትናገራለህ!› እያሉ በተደጋጋሚ ዛቻ ፈጽመውብኛል፡፡
8. አጸያፊ ስድብ እየሰደቡኝ እጄን አስረው በምርመራ ክፍሉ ውስጥ ሰቅለውኛል፡፡ በዚህም ያለምንም ዕረፍት ለሦስት ቀናት እንደ ዕቃ ሰቅለው እራሴን እስክስት አቆይተውኛል፡፡
9. በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከተፈጸመብኝ አካላዊ ማሰቃየት (ቶርች) በተጨማሪ ለ23 ቀናት በቀዝቃዛና በጨለማ ቤት ያለማንም ጠያቂ ታስሬ ቆይቻለሁ፡፡
10. ከደህንነት ቢሮ የመጣ ወረቀት ላይ በግዳጅ አስፈርመውኛል፡፡

ተወልጄ ያደግሁት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ነው፡፡ አፍላ ልጅ ሁኜ ወደአዲስ አበባ በመምጣት ስራ ጀመርሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በዋናነት ትምህርት ለመማር በማሰብ ነው፡፡ በዚህም ቀን ስራ እየዋልሁ በማታ ትምህርት እስከ አስረኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡ የምተዳደረው የራሴን የእንጨት ስራ በመስራት ሲሆን፣ ትዳርም መስርቻለሁ፡፡ ከማገኘው ገቢ እየቀነስሁ ገጠር የሚኖሩ ቤተሰቦቼንም አግዛለሁ፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አባል ሆኜ በሰላማዊና በህጋዊ የፖለቲካ ስራ ተሳትፎ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ እስሩ በእኔ ላይ እስኪደርስ ድረስ በነበሩ ጊዜያት በፊት ቀደም ብለው ለእስር የተዳረጉ የ‹ፖለቲካ እስረኞችን› ወደ እስር ቤቶች በማምራት እጠይቅ ነበር፡፡
(ማስታወሻ፡- አቶ አወቀ አባተ ተፈጽሞብኛል በሚለው ድብደባ ምክንያት በደረሰበት ጉዳት ለወገብ ህመም ተዳርጓል፡፡ በዚህም የተሻለ ህክምና እንደሚያስፈልገው ይናገራል፡፡)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *