‹‹በሰራሁት ስራ እኮራለሁ’ጂ አላፍርበትም፤ ከእስር ስፈታም ስራዬን እቀጥላለሁ›› አቶ ቡልቲ ተሰማ፣ የሰመጉ አባል

ስም፡- ቡልቲ ተሰማ

ዕድሜ፡- 30

አድራሻ፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ

አሁን በእስር የምገኝበት ቦታ፡- ቂሊንጦ እስር ቤት

ለእስር የተዳረግሁበት ምክንያት፡- በሽብር ወንጀል ተጠርጥረሃል የሚል ነው፡፡

በይፋ የተመሰረተብኝ የክስ አይነት፡– በእነ ደረጄ ዓለሙ የክስ መዝገብ በ12ኛ ተከሳሽነት የጸረ ሽብር አዋጁን አንቀጽ 5(ለ)ን በመተላለፍ ‹‹ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት›› የሚል ነው፡፡ አሁን ላይ የክሱ ሂደት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ እየታዬ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ማድመጥ ላይ ደርሷል፡፡

በእስር በምገኝበት ወቅት የሚከተሉት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡

  1. በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እያለሁ ጠያቂ ተከልክያለሁ፤ ቤተሰቦቼን ሳላይ ለቀናት እንድቆይ ተገድጃለሁ፡፡
  2. ቀዝቃዛና ጨለማ ክፍል ታስሬያለሁ፡፡
  3. ክስ ተመስርቶብኝ ቂሊንጦ ከተዛወርሁ በኋላ ደግሞ ጠያቂ ተከልክያለሁ፣ በተለይ ቂሊንጦ የእሳት ቃጠሎ ከደረሰ በኋላ በነበሩት ሳምንታት፡፡
  4. ቃጠሎው መከሰቱን ተከትሎ ወደ ዝዋይ እስር ቤት ተዛውሬ ያለምንም ምንጣፍ ለ12 ቀናት ባዶ ሲሚንቶ ላይ እንድተኛ ተደርጌያለሁ፡፡
  5. ዝዋይ እያለሁ ቀንና ሌሊት እጄ በካቴና ይታሰር ነበር፡፡ ለቀናት በካቴና እንደታሰርኩ ቆይቻለሁ፡፡
  6. በወቅቱ በፖሊሶች ተደጋጋሚ ድብደባ ተፈጽሞብኛል፡፡
  7. ምግብና ልብስ ከቤተሰብ እንዳይገባልኝ ተደርጎ ለቀናት እንድቆይ ተገድጃለሁ፡፡

የኋላ ታሪክ:

ለእስር የተዳረግሁት በ2008 ዓ.ም ነው፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ስሆን በስጋ ከወለድኋቸው አራት ልጆቼ በተጨማሪ ሦስት ችግረኛ ልጆችንም በቤቴ አስጠግቼ አሳድጋለሁ፡፡ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ውስጥ በህጋዊነት በሚንቀሳቀሰው የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በተባለው የሲቪክ ተቋም አባል ሆኜ የሰብዓዊ መብቶችንና የህግ የበላይነትን የሚመለከቱ ስራዎችን ለእስር እስከተዳረግሁበት ጊዜ ድረስ ስሰራ ነበር፡፡

በኦሮሚያ ክልል የነበረውን ህዝባዊ የመብት ጥያቄ ተከትሎ በመንግስት ኃይሎች ይወሰዱ የነበሩ የመብት ረገጣዎችን ህግን ተከትዬ ለምሰራበት ተቋም ሪፖርት አደርግ ነበር፡፡ በሰራሁት ስራ እኮራለሁ’ጂ አላፍርበትም፤ ከእስር ስፈታም ስራዬን እቀጥላለሁ፡፡ በምዕራብ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች የሰመጉን ዓላማዎች በማስረዳት ሰዎች ስለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዲሰሩ፣ ህግ እንዲከበር እንዲታገሉ ትምህርት እየሰጠሁ ነበር፡፡

(ማስታወሻ፡- አቶ ቡልቲ ተሰማ አባል ሆኖ የሚንቀሳቀስበት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) የቀድሞው ኢሰመጉ፣ ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በህግ ተመዝግቦ ለዴሞክራሲ፣ ለህግ ልዕልናና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሰራ ተቋም ነው)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *