ተስፋሚካኤል አበበ፤ “ሆዴ ላይ ሲጋራ እየተረኮሱ ጠብሰውኛል”

ጸሐፊ፡- በላይ ማናዬ

ተስፋሚካኤል አበበ ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ በማሰቃያ እስር ቤቶች ውስጥ አልፏል፡፡ በቅፅል ሥሙ ህርያቆስ እየተባለ በወዳጆቹ ይጠራል፡፡ ከእስር ቤት የማይሽር ጠባሳ ይዞ የወጣው ተስፋሚካኤል የ28 ዓመት ወጣት ሲሆን ነዋሪነቱ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ነው፡፡ ተስፋሚካኤል በፖሊስ ማቆያ ቦታዎች የደረሰበትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደሚከተለው አጫውቶናል፡፡

ጎንደር 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ

ከ2008 ክረምት ወራት ጀምሮ በአማራ ክልል ጎንደር አካባቢ በነበረው ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት፣ ተቃውሞዎች ላይ ተሳትፎ አለህ በሚል ጥር 05/2009 ጎንደር ከተማ፣ ፒያሳ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ፣ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ከተያዘ በኋላ መጀመሪያ ጎንደር አዘዞ ወደሚገኘው 24ኛ ክ/ጦር ወሰዱት፤ “በዚያም ለሁለት ሰዓታት ያህል ሲደበድቡኝ ቆይተው ጎንደር ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ለፖሊስ አስረከቡኝ” ይላል ተስፋሚካኤል፡፡

ተስፋሚካኤል ጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊሶች እጅ እና እግሩን በካቴና አስረው ሁለት ደረቅ ዱላ ሰውነቱ ላይ በድብደባ እንደጨረሱበት ይናገራል፡፡ “እጆቼ እና እግሮቼ ላይ የታሰርኩበትን ካቴና አጥብቀውብኝ የደም ዝውውሬን አዛብተውብኝ ነበር፤ ከታሰርኩበት የሰውነት ክፍሌ ወደ ታች ደም እንዳይደርስ ሆኖ በእጅጉ ተሰቃይቻለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት የእግሮቼ እና እጆቼ ጣቶች ደንዝዘው ለተወሰነ ጊዜ መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር”፡፡

ተስፋሚካኤል ጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ በቆየበት ወቅት ቤተሰብና ወዳጆቹን፣ እንዲሁም የሕግ ባለሙያ እንዳያይ ተደርጎ ለስድስት ቀናት ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ቀናት ምግብ ከውጭ ጠያቂዎች እንዳይገባለት ተከልክሎ ነበር፡፡ በዚያ ጣቢያ መርማሪዎቼ ከፌደራል መንግሥት የተላኩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ነበሩ፡፡ በየዕለቱ ይደበድቡት እንደ ነበርም ተስፋሚካኤል ይናገራል፡፡ “ከጥር 05-13/2009 በዚሁ ጣቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ መብቶቼን ሲረግጡ ካቆዩኝ በኋላ፣ ጥር 13/2009 ሌሊት ወደ አዲስ አበባ፣ ማዕከላዊ እስር ቤት ወሰዱኝ፡፡”

አራት ወራት ‹ሳይቤሪያ› ውስጥ

– በሰዐት እላፊ የፖሊስ ምርመራ

– አካላዊ ማሰቃየት

– ማስፈራራት

ተስፋካኤል አበበ ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ፣ ከአካላዊ እስከ ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን ተቋቁሞ አልፏል፡፡

ተስፋሚካኤል ከጎንደር ወደ ፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ከተዛወረ በኋላ ለአራት ወራት የቆየው በቅዝቃዜው ምክንያት ‹ሳይቤሪያ› በመባል በእስረኞች የሚጠራው የማቆያ ክፍል ‹7 ቁጥር› ውስጥ ነበር፡፡ ‹ሳይቤሪያ› ጨለማ እና ቀዝቃዛ ቤቶች ያሉበት ማቆያ ነው፡፡ ተስፋሚካኤል “ለሁለት ወራት ያክል ማታ ማታ፣ ከሁለት ሰዓት በኋላ ምርመራ ይደረግብኝ ነበር፡፡ በእነዚህ የምርመራ ወራት ሁልጊዜ ይደበድቡኝ ነበር፡፡ ራቁቴን እንድቆም እያደረጉ ይሳለቁብኝ፣ ይሰድቡኝ፣ ይተፉብኝ ነበር፡፡ ማንነቴን እየጠቀሱ ከእነ ቤተሰቤ በጅምላ ይሰድቡኝ እና ያንቋሽሹኝ ነበር፡፡ ደርግ የሚባል ስርዓት በታሪክ ከመስማት ባለፈ አላውቀውም፣ ነገር ግን ‹አንተ የደርግ ርዝራዥ› እያሉ ያሳቅቁኝ ነበር፡፡ መርመሪዎቹ፣ ‹እንገልሃለን› እያሉ ይዝቱብኝም ነበር” ይላል፡፡

“አንድ ጊዜ በማዕከላዊ ለተከታታይ ሦስት ቀናት፣ ለአጭር ጊዜ ያህል ብቻ እያሳረፉ ዘቅዝቀው እየሰቀሉ ውስጥ እግሬን ደብድበውኛል፡፡ እግሮቼን አስረው፣ በመሐል ብረት በማስገባት ያሰቃዩኝ ነበር፡፡ ከተሰቀልኩበት ሲያወርዱኝ ደግሞ በካልቾ፣ በዱላ፣ በጎማ፣ ባገኙት ነገር ሁሉ ይደበድቡኝ ነበር፡፡ ወንበር አንስተው አናቴ ላይ ወርውረው የመቱኝ ጊዜም አለ፡፡ በማስመሪያ ጣቶቼን ለይተው በመቀጥቀጥ አሰቃይተውኛል፡፡ ውስጥ እግሬን በኤሌክትሪክ ገመድ ገርፈውኛል፡፡”

ተስፋሚካኤል ብዙ ጊዜ ምርመራ የሚያደርጉበት ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ እንደ ነበር ያስታወሳል፡፡ ሆኖም አንድ ቀን ግን ፎቅ ላይ ያለ ክፍል ውስጥ ሲደበድቡት ቆይተው፣ ከመሬት በታች (ግራውንድ) ያለ ክፍል ወስደው በኤሌክትሪክ ሾክ ራሱን እንዲስት እንዳደረጉት ይጠቅሳል፡፡ “ሌሊት ሾክ ያደረሱብኝ ዕለት ራሴን ስቼ ቆይቼ፣ ቀን ላይ በእስር ቤቱ ክልኒክ ሆኜ ነው የነቃሁት” ይላል፡፡ ከዚህም በላይ “ብዙ ጊዜ መርማሪዎቹ የሚያጨሱትን ሲጋራ እሳት ሆዴ ላይ እየተረኮሱ ያጠፉብኝ ነበር” በማለት ሆዱ ላይ እስከ ዛሬ የቀረውን ጠባሳ ገልጦ ያሳያል፡፡

“በእነዚህ የማዕከላዊ የስቃይ ጊዜያት አንዲት እህቴ እያለቀሰች እየለመነቻቸው፣ በወር አንዴ ከምታየኝ በስተቀር፣ ቤተሰብም ሆነ ጠበቃ እንዳነጋግር አይፈቀድልኝም ነበር፡፡ አንዲት እህቴን ሊያገናኙኝ ሲሉ እንኳን፣ ‹አንድ ቃል ብትናገር እንገልሃለን› እያሉ ስለሚያስጠነቅቁኝ የሆነብኝን መናገር አልችልም ነበር፡፡”

ተስፋሚካኤል ማዕከላዊ የነበረው የማሰቃየት ምርመራ የቀነሰለት በግዳጅ የተቀበሉትን እና የእሱ ያልሆነን ነገር ጽፈው በግዳጅ ካስፈረሙት በኋላ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከዚያም በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ በሽብርተኝነት ተከስሶ ከማዕከላዊ ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ተዛውሯል፡፡ ቂሊንጦ ለስድስት ወራት ከቆየ በኋላ ችሎት ተዳፍረሀል በሚል ስድስት ወር ተፈርዶበት ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ተዘዋውሮም ነበር፡፡ ከቃሊቲ እስር ቤት ክሳችሁ ተቋርጧል በሚል ከእስር ቤት ተፈትቷል፡፡

ሕይወት ከፍቺ በኋላ

ተስፋሚካኤል እስር ቤት በደረሰበት ጉዳት ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ችግር ተዳርጎ መቆየቱን ይገልጻል፡፡ ከእስር  ቤት ከተፈታ በኋላ ለሦስት ወራት ያህል እንቅልፍ ለመተኛት ይቸገር ነበር፡፡ “አእምሮዬ ይረበሽ ነበር፤ መርማሪዎች ይናገሩኝ፣ ይሰድቡኝ፣ ያንቋሽሹኝ የነበረው ነገር ወደ ሕሊናዬ እየመጣ ያሰቃየኝ ነበር፡፡ ፈቅጄ እና መርጬ ባልተወለድኩበት ማንነቴ ያደረሱብኝ ስድብ በሥነ-ልቦና ጎድቶኛል” ይላል፡፡

“በአካሌ ላይ የደረሰብኝ ጉዳትም ከፍተኛ ነበር፡፡ በተለይ በሲጋራ እሳት ያቃጠሉኝ ሆዴ ላይ ያለው ቁስል አሁንም ያመኛል፤ በጣም ያሳክከኛል፡፡ ታክሜው ነበር፣ ሆኖም ሙሉ መፍትሔ አላገኘሁም” የሚለው ተስፋሚካኤል የሰብአዊ መብቶቹን የረገጡት አካላት ማናቸውም በሕግ ተጠያቂ ስለመሆናቸው የሚያውቀው ነገር ባለመኖሩ፣ “የሰማሁት ነገር የለም” ይላል፡፡ “በሕግ የተጠየቀ አካል ቢኖር ኖሮ ልሰማ እችል ነበር ብየ አስባለሁ፡፡ በእስር ቤት ለተፈጸመብኝ ግፍ የተደረገልኝ የሞራልም ሆነ የገንዘብ ካሳ የለም፤ ስለዚህ ጉዳይ ያነጋገረኝ አካልም የለም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *