“የግለሰብ እስረኛው” ጉለድ መሐመድ

ጸሐፊ፡- በላይ ማናዬ

ሙሉ ሥሙ ጉለድ መሐመድ አሰዌ ይባላል፡፡ የ41 ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡ የሚኖረው በሶማሊ ክልል፣ ጂግጂጋ ከተማ፣ ቀበሌ 06 ውስጥ ነው፡፡ ለእስር ከመዳረጉ በፊት የሶማሊ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ውስጥ ይሠራ ነበር፡፡ ለስድስት ዓመታት ታሥሮ ከተፈታ ዓመት አልሞላውም፡፡ ራሱን “የግለሰብ እስረኛ” እያለ ይጠራል፤ ሙሉ ታሪኩ ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ጉለድ መሐመድ

 

ጂግጂጋ ዞን ማረሚያ ቤት

ያለ ፍርድ እስር

ጉለድ መሐመድ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ሦስት እስር ቤቶች ውስጥ ታስሯል፡፡ መጀመሪያ የታሰረው በ2002 አሚራ (ጂግጂጋ ዞን ማረሚያ ቤት) የሚባል ስፍራ ነበር፡፡ እዚህ ቦታ አንድም ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለስምንት ወራት ታስሯል፡፡ በዚህ እስር ቤት ሲታሰር ምክንያቱ አልተገለጸለትም፡፡ ስምንት ወራት ሙሉ ያለምንም ፍርድ በእስር ከቆየ በኋላ በፍቺ ተሰናበተ፡፡ ፍቺው ግን ዘላቂ አልነበረም፡፡

‹ጄል ኦጋዴን›
– ምግብ፣ የመጠጥ እና ንፅሕና መጠበቂያ ውኃ እጥረት
– ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቅጣት ውሳኔ መቀበል
– ጠበቃ የማግኘት መብትን መነፈግ
– በተጣበበ ክፍል ውስጥ መታጎር

ጉለድ መሐመድ ከአሚራ እስር ቤት ከተፈታ ብዙም ሳይቆይ ግንቦት 13/2003 ላይ በድጋሚ ለእስር ተዳረገ፡፡ ይህኛው እስር ቤት ‹ጄል ኦጋዴን› ይባላል፡፡ ሶማሌ ክልል ውስጥ በጣም አስከፊው እስር ቤት ነው፡፡ እዚህ እስር ቤት ውስጥ ንፁሕ ውኃ ማግኘት አይቻልም፡፡ በቦቴ በየሦስት ቀኑ ከግድብ የሚጣውን ውኃ ነበር እስረኞቹ የሚጠጡት፡፡ ጉለድ መሐመድ “ይህም ሆኖ በጣም ትንሽ ውኃ ነው የሚሰጠን፡፡ ስድብ እና ዛቻ በየጊዜው ይፈፀምብናል፡፡ ቤተሰቦችንም ይሰቃያሉ” በማለት ሁሉንም ጠቅልሎ ለመግለጽ ይሞክራል፡፡

‹ጄል ኦጋዴን› በቤተሰብ መጠየቅ አይፈቀድም፡፡ የሕግ ባለሙያ ማነጋገር አይታሰብም፡፡ ፍርድ ቤት መቅረብ የለም፡፡ ጉለድ መሐመድ እንደሚለው “የተከሰስንበት ምን እንደሆነም የገለጸልኝ አልነበረም፡፡ ‹ጄል ኦጋዴን› ውስጥ ‹ችፊናጆክ› የሚባሉ የማሰቃያ ሥፍራዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሥፍራዎች መጀመሪያ ሲዘጋጁ መታጠቢያ እና መፀዳጃ ቤት እንዲሆኑ ታስቦ ነበር፡፡ በጣም ጠባብ ክፍሎች ናቸው፤ ግማሽ ሜትር በግማሽ ሜትር ቢሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ መታሰር የስቃይ ሁሉ ስቃይ ነው፡፡ መተኛት፣ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ቆመህ መንቀጥቀጥ ነው፡፡ አንዳንዴ ሁለትም፣ ሦስትም ሰዎችን በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ያጉራሉ፡፡ ክፍሉ በጣም ያፍናል፡፡ መሞትም አለ እዚህ ስፍራ፡፡”

‹ጄል ኦጋዴን› በቂ ምግብ አይቀርብም ነበር፡፡ እስር ቤቱ ሙቀቱም ከፍተኛ ነው፡፡ ንፅሕና ለመጠበቅ ውኃ የለም፡፡ ጉለድ “እዚህ እስር ቤት የሚጣሰው የትኛው መብትህ ነው ከምባል፣ የማይጣስ አንድ እንኳ መብት ካለ ተናገር ብባል ይቀለኛል” ይላል፡፡ “አንድም ያልተጣሰ መብቴን አልጠቅስልህም፡፡ የግዳጅ ጉልበት ሥራም ያሠራሉ፡፡ ሦስት ቀን አሠርተው አንድ ሲጋራ ሊሰጡህ ይችላሉ፡፡ ይህንም ካዘኑልህ ነው፡፡ ስቃዩስ ያልፋል፤ እዚህ እስር ቤት ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ‹ጄል ኦጋዴን› ትልቁ የስቃይ ቤት ነው” በማለት በሐዘን ትዝታውን ይገልጻል፡፡

ጉለድ መሐመድ ከታሰረ ጀምሮ አንድም ቀን ፍ/ቤት ቀርቦ እንደማያውቅ ይናገራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ጥቅምት 04/2004 በመኪና ዐሥራ አራት ሰዎችን ይዘውን ወደ ዝዋይ እስር ቤት ሊያዛውሯቸው ጉዞ ተጀመረ፡፡ ማነቸውም ሳይፈረድባቸው ወደ ዝዋይ ፌደራል እስር ቤት እየተዘዋወሩ ሳለ ቆቦ የሚባል ሥፍራ ላይ ከጂግጂጋ የ‹ጄል ኦጋዴን› እስር ቤት ኃላፊዎችን የያዘች መኪና ከኋላቸው ደረሰች፡፡ የ‹ጄል ኦጋዴን› ኃላፊዎች ከመንገድ ዳር ሜዳ ላይ አሰልፈው አስቁመው ሥማቸውን እየጠሩ “እገሌ ይህን ያህል ተፈርዶብሀል” እያሉ ወደ መኪናው መለሱዋቸው፡፡ “ጉለድ መሐመድ ሴት በመድፈር 10 ዓመት ተፈርዶብሃል” ብለው እንደነገሩት ጉለድ ያስታውሳል፡፡ መናገር፣ መከራከር፣ መጠየቅ አይቻልም ነበር ይላል፡፡ ወደ ዝዋይ እየሔዱ ስለሆነ ፍርደኛ ናቸው ለማለት የተደረገ የፈጠራ “ፍርድ” ነው ብለው አስበዋል፡፡ ጉለድ “ይህ በዚህ ዘመን ይፈፀማል ብሎ ማን ያምናል?” ብሎ መልሶ ይጠይቃል፡፡

“መንገድ ላይ ፍርድህ ይህ ነው ብለው ሲነግሩኝ ሳቄ ይመጣ ነበር፡፡ መዝገብ አልያዙም፡፡ ትንሽ ነገር ወረቀት ላይ ጽፈው ፍርዳቸው ይህ ነው ብለው ለዝዋይ እስር ቤት ለማዘዋወር ነው ፍላጎታቸው፡፡ ለእኔ በግሌ የክስ ወረቀትም ሆነ የፍርድ ብይን ወረቀት እጄ ላይ ገብቶ አያውቅም፡፡ በዚህ ሁኔታ በኮንቴነር አፍነው ጭነው ዝዋይ እስር ቤት ወሰዱን፡፡”

ዝዋይ እስር ቤት

ዝዋይ እስር ቤት ለጉለድ የተሻለ ነበር፡፡ “ድብደባ የለም፡፡ ምግብ ከጄል ኦጋዴን ይሻላል፡፡ ከሰው ጋርም መነጋገር እችላለሁ” ይላል፡፡ “በእርግጥ ዝዋይ የሚያነጋግረን የመንግሥት አካል ይኖር ይሆናል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ግን ማንም አላነጋገረኝም፡፡ ያለምንም መዝገብ፣ ያለምንም ማህደር 6 ዓመት ከስምንት ወር በአመክሮ እስሬን ጨርሼ ነው የተፈታሁት” በማለት ቁጭት ግን እንዳለበት አይሸሽግም፡፡

ከፍቺ በኋላ

ጉለድ “እኔ የግለሰብ እስረኛ ነበርኩ፤ የአብዲ ኢሌ የግል እስረኛ ነበርኩ” ይላል፡፡ “አብዲ ኢሌ (በወቅቱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት የነበሩ) እስረኛ አድርጎ አስቀምጦኝ ነበር፡፡ ግፍ ነው የተፈፀመብኝ፡፡ አብዲ ኢሌ ያሰረኝ ለምን ተናገርክ፣ ለምን ተነፈስክ ብሎ ነው፡፡ የእኔ እስር አንዳችም ሕጋዊ መሠረት ሊኖረው ይቅርና የሚመስል ነገር እን’ኳ አልነበረውም፡፡”

ጉለድ ለተፈፀመበት የመብት ጥሰት ምንም የተሰጠው ካሣ የለም፡፡ ጥሰቱን በፈፀሙ አካላት ላይ የሕግ ተጠያቂነት መኖሩንም እንደማያውቅ ይናገራል፡፡ “ሕዝቡ ግፊት ባያደርግ ከእስር አልፈታም ነበር” ብሎ ያምናል፡፡ “በበኩሌ ካሣ ይደረግልኛል ብዬ አላስብም” ይላል፡፡ ጉለድ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ከጅግጅጋ ከተማ እንዲወጣ አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ክትትል ነበረበት፡፡ ከመታሰሩ በፊት የመንግሥት ሥራ ነበረው፤ ከፍቺ በኋላ ግን ሥራ አጥ ሆኖ ቆይቷል፡፡

(ጉለድ መሐመድ በቅርቡ ከእስር ተፈቶ ጂግጂጋ ከተማ ይኖራል፡፡ ጉለድ የሁለት ልጆች አባት ነው፡፡)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *