ያሬድ ሑሴን – ከቂሊንጦ ቃጠሎ እስከ ሸዋ ሮቢት ስቃይ

ጸሐፊ፡- አጥናፉ ብርሃኔ

በነሐሴ 26፤2008 በቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከእስረኛ ቤተሰቦች ምግብ እንዳይገባ መደረጉ በእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ መናፈስ ጀመረ። ጉዳዩ ያሳሰባቸው ታራሚዎች በየክፍሉ የሚገኙ የእስረኛ ተወካዮችን ጉዳዩን እንዲያጣሩላቸው ቢጠይቁም ከማረሚያ ቤቱ አስተዳደሮች በቂ ምላሽ ሳያገኙ ቀሩ። ነሐሴ 28፣2008 የእስር ቤቱ አላፊዎች በለጠፉት ማስታወቅያ “የአተት ወረርሽኝ በማረሚያ ቤቱ በመግባቱ ከቤተሰብ ለእስረኛው የሚገባ ምግብ ተከልክሏል” የሚል ነበር። በዚህ የተበሳጩ ታራሚዎች ከማረሚያ ቤቱ የሚቀርብላቸውን ምግብ አልበላም በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀመሩ። የእስረኞቹ የቁጣ ስሜት ያላማራቸው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደሮች እስረኛው ከተወሰነ ክልል እንዳያልፍ ወደ ቤተሰብ መጠየቂያ የሚወስደውን የኮሪደር በር በሰንሰለት ቆለፉት።

በወቅቱ ከታሳሪዎቹ አንዱ የሆነው የ26 አመቱ ያሬድ ሁሴን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን ሁለት ተብሎ በሚጠራው የእስረኛ ማቆያ 7ኛ ቤት ውስጥ ነበር። በነፍስ ማጥፋት ተጠርጥሮ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ የነበረው ያሬድ ሁሴን በወቅቱ ስለተፈጠረው ነገር ሲያስረዳ። “ማረሚያ ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ የተቆጡ ታራሚዎች ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ ጩኸት ማሰማት ጀመሩ፤ በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ሦስቱም ዞኖች ከፍተኛ ጩኸት ይሰማ ነበር” ይላል። ያሬድ ከነበረበት ዞን 2 ከሚገኙ ቤቶች ውስጥ 5ኛ ቤት የሚባለው በእሳት ተያያዘ፤ አንዳንድ ታራሚዎች ዩኒፎርማቸውን አውጥተው ሜዳ ላይ መጣል ጀመሩ። ወድያው የተኩስ ድምፅ መሰማት ጀመረ። አስለቃሽ ጭስ ወደ ዞኑ በመወርወሩ ምክንያት እስረኞች መተያየት አቃታቸው፤ ከ5ኛ ቤት የጀመረው እሳት በኮርኒሱ ውስጥ በመሄድ በዞን ሁለት ያሉ ስምንቱም ቤቶች በእሳት ተያያዙ።

በቤት ውስጥ የነበረው እስረኛ ከጥይት ለማምለጥና በአስቃሽ ጭስ ምክንያት እይታው ስለተጋረደ መሬት ለመሬት እየተንፏቀቀ በዞኑ ቅጥር ግቢ ዳር ዳር በሚገኝ ቀጭን ቱቦ ውስጥ ሕይወቱን ለማዳን በዳሰሳ መሰግሰግ ጀመር። ከሰባተኛ ቤት መሬት ለመሬት እየተንፏቀቀ የወጣው ያሬድ ሕይወቱን ከጥይት ለማዳንና ከአስለቃሽ ጭስ ለማምለጥ፣ ንፁህ አየር ለማግኘት 6ኛ ቤት ሥር የሚገኝ ቱቦ ውስጥ እራሱን ወሸቀ። የጥይት ድምፅ ካለማቋረጥ ይሰማ ነበር፤ ዞኑ በጭስ ተሸፍኗል። ሁሉም ሕይወቱን ለማዳን ወደ መውጫው ኮሪደር ይሮጣል፤ ሰው በጥይት ተመቶ ሲወድቅ ይታያል። ያሬድ እየተንፏቀቀ ወደ ኮሪደሩ አዘገመ “እኔና ጓደኛዬ ወደ ኮሪደሩ እየተንፏቀቅን መሔድ ጀመርን። ቢንያም ይባላል፤ መቅዱሴ (ገበታ አብሮኝ የሚቋደስ ሰው) ነበር። እዮብ ገመቹ የሚባል ፖሊስ ተኩሶ እግሩን መታው፤ ኮሪደሩ ላይ ቆሞ ወደ ውስጥ ነበር የሚተኩሰው፤ ፊት ለፊቴ እያየሁት ጓደኛዬ ድጋሚ ደረቱን በጥይት ተመቶ ሞተ፡፡ ከእሳቱ ለማምለጥ ወደ ቤተሰብ መጠየቂያው የሮጡ እስረኞች ቆጥ ላይ ባሉ ፖሊሶች ጥይት ተተኩሶባቸው ተገድለዋል” ይላል ያሬድ በወቅቱ ያየውን ሲያስረዳ።

የያሬድ ስቃይ

ያሬድ በእስር ቤት ውስጥ ስቃይ ሰውነቱ ላይ ካረፉበት ጠባሳዎች አንዱ

ከእሳቱና ከጥይቱ የተረፉ እስረኞች በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ጫማዎቻቸውንና የደረቡትን ልብስ እንዲያወልቁ እየተደረገ በባዶ እግራቸው ከአዲስ አበባ 125 ኪሜ ርቀት ወደሚገኘው ዝዋይ የፌደራል ማረሚያ ቤት ተጭነው ተወሰዱ። ታራሚዎቹ ዝዋይ ደርሰው ከመኪና እንደወረዱ ፖሊሶች ቀጥታ ወደ ዱላ ገቡ። “ፒስታ መንገድ ላይ እያሯሯጡ ይደበድቡን ነበር፤ ለስምንት ቀን ያህል ሲሚንቶ ላይ ውኃ እየተደፋብን እንድናድር ተደርገናል። በስምንኛው ቀን ለሊት ላይ በር ተደብድቦ ፖሊሶች ገቡ፤ ‘አሁን የምትጠሩ ቀስ ብላችሁ ድምፃችሁን አጥፍታችሁ ውጡ’ አሉን ልንረሸን ነበር የመሰለኝ፤ 54 ልጆች ተጠርተን ወጣንና ወደ ቂሊንጦ አመጡን” ይላል ያሬድ ሁሴን። አእስረኞቹ ቂሊንጦ ለአንድ ሰአት ያክል ከቆዩ በኋላ ወድያው ወደ ሸዋ ሮቢት የፌደራል ማረሚያ ቤት ተወስደው ለከፍተኛ ምርመራና ስቃይ ተዳርገዋል። እስረኞቹ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት እንደደረሱ ለሁለት ታስረው እንደከረሙ ያሬድ ይናገራል። “ለሁለት ነው ያሰሩን፤ ሽንት ቤት መጠቀም አልቻልንም ነበር፤ ለቀናት እጄ ከአንዱ እስረኛ ጋር ታስሬ እንድፀዳዳ ተደርጌለሁ፤ መቆየት አይቻልም ነበር፤ ቁጭ ባልንበት ፖሊስ እየመጣ ‘ተነስ’ እያለ ይደበድበን ነበር፤ ሱሪያችንን እንኳን መታጠቅ አልቻልንም”

ምርመራ በሸዋ ሮቢት

ያሬድ ሑሴንን ጨምሮ በሸዋ ሮቢት የተገኙ ታራሚዎች ለከፍተኛ ድብደባ ተዳርገዋል። ‘የቂሊንጦን ማረሚያ ቤት በእሳት ያያያዛችሁት እናንተ ናችሁ’ እየተባሉ ሊቋቋሙት የማይችሉት ስቃይ ውስጥ ገብተው ነበር። በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ረብሻ በተነሳ ሰዓት የማረሚያ ቤቱን ንብረት አውድማችኋል ከተባሉትና ምርመራ ሲደረግባቸው ከነበሩት ውስጥ አንዱ ያሬድ ሁሴን ነበር። ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጡ መርማሪ ፖሊሶች በሸዋ ሮቢት ተገኝተው ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ በእስረኛው ላይ ሲፈፅሙ እንደነበር ያሬድ ይናገራል። “ከታስርኩበት ክፍል አውጥተው ወደ ምርመራ ቦታ ወሰዱኝ፤ ወድያው እጄን በካቴና አስረው እንጨት ላይ ካያያዙት በኋላ አንድ እግሬን በገመድ መጎተት ጀመሩ፤ ‹Nike› ተብሎ የሚጠራው አስተሳሰር ነው፤ በዚህ ሰዐት ሙሉ ክብደቴ በካቴና በታሰረው እጄ ላይ ስላረፈ እጄ ተቆርጦ ሊወድቅ የደረሰ እስኪመስለኝ ድረስ ነበር ሕመሙ የተሰማኝ። በወቅቱ መስታወት ሰብረሃል ነበር የሚሉኝ፤ ስቃዩ ስለበዛብኝ አዎ ሰብሬአለሁ ብዬ አመንኩ።” ይላል ያሬድ የሸዋ ሮቢት ቆይታውን ሲያስረዳ።

የ26 ዓመቱ ወጣት ያሬድ ሑሴን በእስር ቤት ቆይታው ብዙ ጠባሳዎችን ይዞ እንደወጣ ይናገራል፡፡

ለያሬድ ምርመራው በዚህ አላበቃም። ከቆይታ በኋላ ሰው ገድለሃል ወደሚል ከበድ ያለ ምርመራ ውስጥ እንዲያልፍ ተገዶ ነበር። በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተነሳውን እሳትና ጭስ ለማምለጥ እየተንፏቀቁ ሲሔዱ እዮብ ገመቹ በተባለ ፖሊስ በጥይት ተመቶ የተገደለውና ጓደኛው የሆነውን ቢንያም አሰፋን ገለሃል ወደሚል ምርመራ ተሻገረ። ያሬድ ሊቋቋመው ወደማይችለው ማሰቃየት ውስጥ በመግባቱ የገዛ ጓደኛውን እና ሎሌች 5 ሰዎችን ገድያለሁ ብሎ እንዳመነ ይናገራል፡፡ “ስቃዩ ከባድ ነበር፤ ሦስት ቀን በተከታታይ አሰቃይተውኛል። እጄንም እግሬን በሰንሰለት አስረው ሰቅለውኝ ይሄዳሉ፤ በተደጋጋሚ እራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፤ ምግብ አልበላም ብዬ የርሃብ አድማ አድርጌ ነበር። መጨረሻ ላይ አንድ የፖሊስ አባል ‘ይገሉሃል ብትበላ ይሻልሀል’ ሲለኝ ነው መብላት የጀመርኩት። ‘የእስር ቤቱን በር አንተ ዘግተህባቸው ነው እስረኞቹ ተቃጥለው የሞቱት’ ብለህ እመን ነበር የሚሉኝ። አዲስ እየተሠራ ወዳለው ማረሚያ ቤት ሠራተኞች የሌሉ ቀን እኔ እና ሸምሱ ሰኢድ የሚባል ሌላ ታሳሪን ወስደውን ከመኪና ጋር እግራችንን አስረው ሲጎትቱን ነበር፤ የፍሎረሰንት መብራት አምፖል በእሳት በማጋል የብልታችንን ፍሬ ሲተኩሱት ነበር። በጣም ነበር የሚያቃጥለው። ስቃዩ ልቋቋመው የማልችል ስለነበር የፈለጉትን ነገር ለማመን ወሰንኩ። መጀመሪያ 10 ሰው ገድለሃል ነበር ያሉኝ፤ ሰው አያምነንም ብለው ቁጥሩን ወደ 6 ቀነሱት” ይላል በአሰቃቂ ሁኔታ ምርመራ ሲደረግበት የነበረው ወጣት ያሬድ ሁሴን።

ከሸዋ ሮቢት መልስ

ምርመራ እንዳለቀ ወደ ቂሊንጦ የተመለሰው ያሬድ ክስ ሳይመሠረትበት ብዙ ቆይቶ በመጀመሪያ የተከሰሰበትን የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ ከፍተኛው ፍርድቤት ነፃ ብሎት ነበር። ነገር ግን በእስር ቤቱ አሠራር መሠረት ከፍርድ ቤት መፈቻ ወረቀት መጥቶለት ከቅሊንጦ እስር ቤት እቃውን ይዞ በመውጣት ላይ እያለ የፌደራል ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ) ፖሊሶች በር ጋር ጠብቀው ወደ ማዕከላዊ ወስደው ሳይፈቱት ከወር በላይ በጨለማ ቤት ውስጥ አስቀምጠውታል። ያሬድ እዛው በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እያለ 6 ሰዎችን በመግደል ‘ከባድ የሰው መግደል ወንጀል’ ክስ ተመስርቶበት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዳግም ተመልሶ ለሁለት ዓመታት ክሱን ሲከታተል ቆየቶ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ክሱን የሚያቋቁም ማስረጃ በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቱ ሐምሌ 24፤ 2010 ክሱን አቋርጦ ተከሳሽ ያሬድ ሔሴንን በነፃ አሰናብቶታል።

አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ያሬድ ሑሴን፣ አሁን ከእስር ተፈትቶ “ነፃ ሰው” ቢሆንም ያሳለፈው ስቃይ በሰውነቱ ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *